የመንግሥት ሠራተኞች የዳታ ማረጋገጥና የዲጂታል መንግሥት (E-Governance) አፈፃፀም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ::******አዲስ አበባ | ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፡ የመንግሥት ሠራተኞች የፐርሶኔል ዳታ ማረጋገጥ እና የዲጂታል መንግሥት (E-Governance) ትግበራ አፈፃፀም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ ከ400 በላይ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተወከሉ ሚኒስቴር ድኤታዎች፣ የተለያዩ ሥራ ከፍሎች ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር መኩሪያ ሀይሌ በመክፈቻ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ግልጽ፣ ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ለመገንባት የመረጃ ጥራትን ማረጋገጥና ዲጂታላይዜሽንን ማፋጠን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። ተቋማትም በአደረጃጀት ማሻሻያ፣ በሰው ኃይል ብቃት፣ በዲጂታላይዜሽን እና በአገልግሎት ማሻሻል ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።በመድረኩ የኢ-ጎቨርናንስ አፈፃፀም፣ የመንግሥት ሠራተኞች ዳታ ማረጋገጥ፣ የአገልግሎት ምደባና ኮዲንግ፣ እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎት ምዝገባ ፖርታል እድገት ዙሪያ ገለጻዎች ቀርበው ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።በመጨረሻም የመንግሥት ሠራተኞች የዳታ ማረጋገጥ ሥራን በተያዘው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ፣ የልዩ ሠራተኛ መለያ ቁጥር (Personnel Identification Number) አተገባበርን ለማጠናከር እና የኢ-ጎቨርናንስ ትግበራን ወደ ሙሉ አፈፃፀም ለማሸጋገር ተግባራዊ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።



